ፍልስፍና ብዙዎች ሱሰኛ የኾኑበት የዓለማችን የዕውቀት የቸዝ ጨዋታ ነው፡፡ ይኽንንም የቸዝ ጥበብ ባለምጡቅ አእምሮ ፈላስፎች ሠርተውታል/ፈጥረውታል፡፡ ጨዋታውም በአመክንዮ ተጠየቅ (Logic) እንዲካሔድ ተደርጎ ተቀርጽዋል፡፡ የፍልስፍና ምሁራኑም የቀድሞ ሠሪዎቹን በማድነቅና በማዳነቅ ወይም በመተቸት እየተጫወቱት ኖረዋል/ይኖራሉ፡፡ በጨዋታው ንግሥቷን እውነት ለማግኘትም የማሰብ አቅማቸውን (ዕውቀታቸውን) ኹሉ ተጠቅመው ሲወዳደሩ (ሲከራከሩ) ጊዜያቸውን ይፈጃሉ፡፡ ይኽም ጨዋታ የሚካሔደው በቋንቋ ነው፡፡ ኾኖም ብዙዎቹ ምሁራን በቋንቋ አጠቃቀም ስልት የጨዋታውን ውስብስብነት በመጨመር ያልሠለጠነ ሰው (የፍልስፍና ትምህርት ያልተማረ) የማይደርስበት ክልል ሠርተው አስቀምጠውታል፡፡ እነሱ ግን አጨዋወቱን በመሠልጠንና በማሠልጠን ይለማመዱና የመባልን ይወስዳሉ፡፡ ስለኾነም ማዕረጋቸውንና የሠለጠኑበትን ክልል ለማስጠበቅ የጨዋታውን ሜዳ በሥነ አመክንዮ አጥር ስላጠሩት ማን ደፍሮ ይግባበት?...
... በቸዝ ጨዋታ ሥልጠና የተጠመዱ ብዙዎቹ አካዳሚዊ የፍልስፍና ምሁራንም ሥልጠናውን የወሰዱት ፍልስፍና በተሠራበት በምክንያት ዘይቤ ብቻ ስለኾነ ፍልስፍና ቅኔነት የሌለው ጥበብ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ምሁራኑን የሥልጠና ተፅእኖ ይዟቸው እንጂ የፍልስፍና ጥበብ የሚገኘው በቅኔነት ተቃኝቶ መኾኑ እርግጥ ነው፡፡ ችግሩ ግን በቸዝ ጨዋታ የማመክነይ (የምክንያታዊነት) ሕግ ብቻ መሸበብና ቅኔነትን ከዐለማወቅ የሚመነጭ መኾኑ ላስተዋለው ሰው ግልጽ ይኾንለታል። ፍልስፍና በተፈጥሮው ቅኔነት ባይኖረው ኖሮም ተራ ጥበብ ኾኖ ይቀር ነበር፡፡ ማመክነይ ብቻ እንጂ መደነቅ የፍልስፍና መሠረት መኾን አይችልም ነበር፡፡ ይኽንን ለመረዳት ምናልባት የፍልስፍናን መሠረታዊ ዕሳቤዎች ከቅኔነት ተፈጥሮ ጋር በማነጻጸር ማየት ይጠይቅ ይኾናል፡፡
ለምሳሌ የፍልስፍና ጥበብ